ሾንኬ መንደር/ Shonke old Mosquee village -->

ሾንኬ መንደር/ Shonke old Mosquee village





የሾንኬ መንደር በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር በደዋ ጨፋ ወረዳ በጅሮታ ቀበሌ የሚገኝ ነው:: መንደሩ ከብሄረሰብ አስተዳደሩ ርዕሰ መዲና ከሚሴ በስተምስራቅ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል:: መንደሩ ካለፉት 900 ዓመታት በላይ ደምቆ የኖረ ነው፤ በመንደሩ ውስጥ የሚገኘው ጥንታዊ መስጊድ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ተቋም በመሆንም አገልግሏል::


የሾንኬ መንደርና መስጊድ ለየት ያለ የስነ-ህንፃ አሠራር በተራራ ላይ የአፓርታማ ቤቶችን የሚመስል ነው::በሾንኬ ውስጥ ሶስት መስጊዶች ሲኖሩ ዋናውና በዕለተ አርብ ሁሉም በአንድ ላይ ለጸሎት የሚገናኙበት በመንደሩ አናት ላይ የሚገኘውን መስጊድ ነው::


በመስጊዱ አዛውንቶች እንደሚናገሩት ከሀገር ውስጥ ከጅማ፣ ከጉራጌ፣ ከሀረር፣ ከአርሲና ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም ከውጭ ሀገር በተለይም ከየመን እየመጡ ይማሩ እንደነበር ይገልጻሉ::
ለሾንኬ መስጊድና መንደር ምሥረታ ቅድመ ሁኔታ የነበረው በዚሁ በሾንኬ አካባቢ ወደ ምሥራቅ 6 . ርቀት ላይ የሚገኘው የጦለሀ መንደርና መስጊድ መመስረት ነበር::

 

 የጦለሀ መስጊድና መንደር የተመሠረተው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዕድሜ ባለፀጋዎች እንደሚሉት በግምት ከዛሬ 900 ዓመት በፊት ከሾንኬ መንደር 34 ዓመት ቀደም ብሎ ነው::የጦለሀን መስጊድ የመሠረቱትኩሉባስየተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ ከእርሳቸው ጋር ፈቂ አህመድ የተባሉ ሸህም አብረው ይኖሩ እንደነበር ይነገራል:: ሁለቱም ግለሰቦች ከአርጎባ ብሔረሰብ የወጡና የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው በአሁኑ ሾንኬ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩ ከሌላ የብሔረሰብ አባላት ጋር በየጊዜው ግጭቶች እንደነበሩ የዕድሜ ባለፀጋዎች በትውልድ ያገኙትን ታሪክ ይናገራሉ::ግጭቶቹ ተደጋጋሚና የተጠናከሩ ስለነበሩ ከብዙ ሙከራ በኋላ በሾንኬ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ሌሎች የጎሳዎች አባላት ጦለሀን በማጥቃ ኩሉባስን ገደሏቸው::


በዚህን ጊዜ ጦለሀ ውስጥ ሸህ ፈቂ አህመድ ቀሩ:: እንደ አዛውንቶች አነጋገር ሸህ ፈቂ አህመድ ጥቃት ያደረሱባቸውን ከመመለስና ከመከላከል ባሻገር የኩሉባስንደም ለመመለስ አስፈላውን ዝግጅት ያደርጉ ነበር:: ሸህፈቂ አህመድ አስፈላጊውን ዝግጅት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሾንኬ በመዝመት የኩሉባስ ገዳዮች የሆኑትን ጎሳዎች በማጥቃት ሾንኬን አስለቅቀው ያዙ::
በዚህም የሾንኬ መንደርና መስጊድ መመስረት ቻለ::


የመጀመሪያው የሾንኬ መስጊድ መስራች ሸህ ፈቂአህመድ ናቸው:: ሸሁ የአርጎባ ብሄረሰብ አባል ሲሆኑ በመጀመሪያ ወደ ጦለሀ የመጡት በመጅድ በኩል አምዞሉ ተብሎ ከሚጠራ ተራራማ አካባቢ እንደነበር ይነጋራል:: ይህ አምዞሉ የሚባለው አካባቢ በአሁኑ አከላለል በአፋር ክልል ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው::
የሾንኬ መስጊድ የተመሰረተው እንደአዛውንቶች አባባል ከዛሬ 900 ዓመት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል:: ለዚህ ጊዜ አዛውንቶች በቃል ከሚሰጡት በስተቀር የጽሑፍ ምንጮች ማግኘት አልቻልንም::

 

 

ሸህ ፈቂ አህመድ የሾንኬ መስጊድ ከመሠረቱ በኋላ ሰልሀቦ የሚባሉት የእርሳቸው ዘሮች /ጎሳዎች/ አየመጡ በዚሁ በመስጊድ መንደሩን እያሳደጉት ሄደ:: ከጊዜ በኋላም የአርጎባ ብሔረሰብ የሆኑ ሌሎች ጎሳዎች እየመጡ በመጨመር መንደሩ እያደገና የህዝቡም ቁጥር እየጨመረ እንደሄደ አዛውንቶች ይናገራሉ::


ሸህ ፈቂ አህመድ በሾንኬ መስጊድ በኖሩበት ዘመን የሠሯቸውን ዝርዝር ሥራዎችና የሕይወት ታሪካቸውን በሚመለከት በቂ ማስረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም::ከሸህ ፈቂ አህመድ በኋላ በሾንኬ መስጊድ ውስጥ ብዙሙደረሶች / አስተማሪዎች/ እንደኖሩይነገራል:: ከነዚህም ውስጥ ሀጂ ቀርቦ መሐመድ ሸህ ዘይኑ የሚባሉ ነበሩ::ከነዚህም ወደ መጨረሻው የነበሩት ሸህ ዘይኑ ነበሩ::

 

 

 ሸህ ዘይኑ የሾንኬን መስጊድ ለብዙ ጊዜ ያስተዳድሩ የእስልምና ትምህርት ያስተምሩ እንደነበር መረጃች ይጠቁማሉ:: ከሸህ ዘይኑ በመቀጠል ወደ ሾንኬ መስጊድ የመጡት ጅሀር በን ሀይደር የተባሉት ሸህ ናቸው:: ሸህጅሀር ቢን ሀይደር ወደ ሾንኬ መስጊድ ከመጡ በኋላ በአካባቢው ህዝብ በነበራቸው ከበሬታና ፍቅር የተነሳ አዲስ ስም ተሰጣቸው ይህም ስም ሸህ ሾንኬ / አባዬ ሾንኬ/ የሚል ነበር:: ከዚህ በኋላ በህይወት ዘመናቸው ከአረፉም በኋላ እስከ አሁን ድረስ የሚጠሩት ሸህ ሾንኬ /አባዬ ሾንኬ/ እየተባሉ ነው:: መስጊድም የሸህ ሾንኬ መስጊድ ተብሎ ተሰየመ::

 

 ሸህ ሾንኬ / ጅሀር ቢንሀይድሮ/ የተወለደው ግስርስር አካባቢ ልዩ ስሟ ደኜ አገር ተብላ በምትጠራው ቦታ እንደሆነ ይነገራል:: ይህ ቦታ በአሁኑ አከላለል በደቡብ ወሎ ዞን ሰሜን ቃሉ ውስጥ ይገኛል:: በዚሁ በተወለዱበት አካባቢ ካደጉና የእስልምና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የእስልምና ማዕከል ወደ ነበረችው ይፋት ሄዱ:: ይፋት ውስጥ የቆዩበት ጊዜ በትክክል ባይታወቅም አረቢያ የሚባል ትምህርት /የአረብኛ ቋንቋ ትምህርት/ ተከታትለዋል::ከዚህ በኋላ ወደ ወሎ በመመለስ ባቲ አካባቢ ልዩ ስሙ ጎጃም በሚባል ቦታ በመቀመጥ ፍቂህ የሚባል ትምህርት ተከታትለዋል::

 

ከዚህ ትምህርት በኋላ ቃሉ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ በመቀመጥ የተደሪስ ትምህርት /የማስተማር/ቀርተዋል:: ሸህ ሾንኬ ረዘም ላለ ጊዜ ደዌ ውስጥ ተቀምጠው በሚያቀሩበት ወቅት ወደ ሾንኬ በመምጣት በወቅቱ የሾንኬን መስጊድ ይመሩ የነበሩትን ሸህ ዘይኑን እየዘየሩ ይመለሱ እንደነበር አዛውንቶች ይናገራሉ::

 

ሸህ ሾንኬ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደዌን በመልቀቅ ተጠቃለው ወደ ሾንኬ መስጊድ መጡ:: ወደ ሾንኬ ከመጡ በኋላና የመስጊድ መሪ የነበሩት ሸህ ዘይ ከአረፉ በኋላ የሾንኬ መስጊድ የመሪነት ቦታና የማስተማር ስራ ተረከቡ::


የሾንኬ መስጊድ የአካባቢውን ሙስሊም አስተማሪና ለፀሎት ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥና የውጭ አገርም ጭምር የእስልምና ኃይማኖት ማስተማሪያ ማዕከል እንደነበረች አዛውንቶች ከአባቶቻቸው ያገኙትን ታሪክ መሠረት በማድረግ ይናገራሉ::


የሾንኬ መንደር የቤቶች አሠራር በመንደሩ ውስጥ ያሉ ቤቶች ግድግዳቸውን በባለ ሙያዎች እየተመራ አራቱም ማዕዘን ውብ በወኑ ድንጋዮች እየተዳረዳረ የተመረጣ አፈር በማቡካት እንደ ሲምንቶ በማጣበቂየነት (በአያያዥነት) ግድግዳው እንዲገነባ ይደረጋል:: ውሃ ልኩ የተጠበቀ እንዲሆን ግንቡ በአንድ ጊዜ እንዲጠናቀቅ አይፈለግም፤ አየዋለ እያዳር መስተካከሉ ከተረጋገጠ በኃለ የግድግዳውን ግንባታ ይጠናቀቃል::የቤቱ ጣረያ ከእንጨት ባለዎት ላይ ጋድም በመጫን ቅርጫፍትና ቅጠሎችን በላዩ ላይ በመረበረብ ኮርት ከላይ በማድረግና የተመረጠ አፈር ከላይ በመዳልደልና ዝናብ እንዳያስገባ ከእንጨት የተሳራ መፍሳሽ በመስራት ያንጻሉ:: የውጭ ጣራውን ለመናፈሻነት፣ እህል ለማስጫ ይገለገሉበታል::

 

 የቤቱ የውስጥ ገጽታ የአብዛኞቹ ቤቶች የውስጥ ክፍል የመቀመጫና የመኝታ ክፍሎችም በግድግዳ የተለዩ ሲሆን በኖራ አፈር ምርጊት የተለሰኑ በመሆናው ንፅና ማራኪ ናቸው:: የማረፊያ ክፍሎቻቸው መደብ የተሠራለት ሲሆን እንደ ግድግዳዎቹ ሁሉ በኖራ አፈርና በእበት የተለቀለቀ ስለሆነ ንፅህናው በሲሚንቶ ሊሾ ከተደረገ የከተማ ቤት የሚያንስ አይደለም:: እያንዳንዱ ቤት አንድ ወይም ሁለት በር አለው:: አንድ ቤት ከሌላው በዚህ ይለያል:: በሾንኬ መንደር በዚህ ዓይነት የተሠሩ 143 በላይ ቤቶች ሲኖሩ 2 ትንንሽና 1 ትልቅ መስጊድ በጠቅላላው 3 መስጊዶች ይገኛሉ::

 

ትልቁ መስጊድ የሚገኘው ከመንደሩ መካከልና የመጨረሻውን የመንደሩን ከፍታ ይዞ ሲሆን የመንደሩ ቁንጮ / ጫፍ/ ነው ማለት ይቻላል:: ይህ መስጊድ ቁመቱ 3 ሜትር፣ ስፋቱ 289 ካሬ ሜትር ውፍረት 40 . ነው:: የሾንኬ መንደር መጽሀፍ እንዳተተው የሾንኬ መልከ አምድራዊ አቀማመጥ እጹብ ድንቅ የሚባል ነው፤ ማኅበረሰቡም የራሱን ባህልና ቋንቋ ወደ ኋላ ሳይል ቀደም ሲል የነበረውን የስልጣኔ አሻራ ዛሬ ድረስ የተለየ አፓርታማ በሚመስል ሁኔታ ላይ በምስክርነት በማቆት ህያው ምስክር አድርገው አዝልቀውታል::


ከዚህም ባለፈ ሾንኬዎች መልካም የሆነ የእንግዳ ተቀባይነታቸው ሳይደነቅ አይታለፍም:: ሆኖም ግን ይህ የሾንኬ ታሪክ ከሀገር አልፎ በዓለም በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ መስፈር የሚችል ነው::

የሾንኬ መንደር መጽሀፍ በኩር ግንቦት 17 ቀን 2012 . ዕትም
በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኩር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
http://www.amharaweb.com/Bekur ላይ ማግኘት ይችላሉ።




buttons=(Accept !) days=(20)

Our website uses cookies to enhance your experience. Learn More
Accept !
To Top