ውብ እና ማራኪ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድርን የታደለችው አርባ ምንጭ ከተማ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋሞ ዞን ዋና መቀመጫ እና የተለያዩ የክልል ቢሮዎች መገኛ ስትሆን ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻም ናት፡፡
ስያሜዋን ያገኘችው በከተማዋ ከሚገኘው ጥቅጥቅ ደን በሚፈልቁ 40 ምንጮች ነው፡፡ የቀድሞ መጠሪያዋ "ጋንታ ጋሮ" ይባል እንደነበር ይነገራል።
አርባ ምንጭ የጋሞ አባቶች መገለጫ የሆነው የእርቅ ስርዓት "ዱቡሻ" መፍለቂያ፣ የእንግዳ አክባሪ ህዝብ መገኛ እና ተከባብሮ በፍቅር የመኖር ተምሳሌት "ዮ መስቀላ" በድምቀት የሚከበርባት ናት።
አርባ ምንጮችን ጨምሮ በእግዜር ድልድይ፣ አባያ እና ጫሞ ሐይቆች፣ በአዞ ራንች፣ በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ እና በሌሎች የቱሪዝም መስህቦች የተከበበች ድንቅ ከተማም ናት አርባ ምንጭ፡፡ በዓሳ እና በፍራፍሬ ምርቶች ትታወቃለች፡፡ ከፍራፍሬ ምርቶቿ የሙዝ ምርትን ጨምሮ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ እና ፖም ይጠቀሳሉ፡፡
አርባ ምንጭ የአሁኑን የአየር ማረፊያን ጨምሮ የባህር ትራንስፖርት የሚሰጥባት ከተማ ናት።
ከተማዋ ከመዲናችን አዲስ አበባ 505 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 285 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ሲሆን ቆላማ የአየር ንብረት አላት።
የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዕከል የሆነውን የሴቻ ከተማን እና የገበያ አካባቢ የሆነውን የሲቀላን ከተማ አቅፋ የያዘች ውብ ከተማ ናት።
በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ በከተማዋ ታዋቂ ሆቴሎች እና ሎጅዎች የሚገኙ ሲሆን የኃይሌ ሪዞርትን ጨምሮ ፖራዳይዝ ሎጅ፣ ቱሪስት ሆቴል፣ ሞራ ሀይትስ ሆቴል እና ሌሎችም ይገኛሉ።
በከተማዋ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና የአርባ ምንጭ ፖሊቴክኒክን ጨምሮ የተለያዩ ኮሌጆች እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ።
ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ ለሚደረግ ጉዞ ሁለት አማራጮች ያሉት ሲሆን ከአዲስ አበባ በቡታጅራ እንዲሁም ከአዲስ አበባ በሻሸመኔ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የአውሮፕላን ትራንስፖርት የጉዞ አማራጭ አላት።
በዚህች ድንቅ እና ማራኪ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ ወይም በተለያየ አጋጣሚ ሄዳችሁ ልዩ ትዝታ ነበረን የምትሉ ትዝታችሁን አጋሩን።