የሱባ መናገሻ ጥብቅ የመስህብ ሥፍራ የብዝሃ ተፈጥሮ መገኛ እና
ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው። ይህ ውብ የተፈጥሮ መስህብ በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ አቅጣጫ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በአፍሪካ ዕድሜ ጠገቡ ጥብቅ ደን በአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመነ መንግሥት
ከ1434 እስከ 1468 ዓ.ም በንጉስ ትዕዛዝ መጠበቅ እንደጀመረ ይነገራል፡፡
ይህ በተለያዩ የብዝሃ ህይወት ስብጥር የታደለው የሱባ መናገሻ
በዕድሜ ጠገብ ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ትልቁ የደን ስፍራ በወጨጫ ተራራ ሥር የሚገኝ ውብ የቱሪዝም መደረሻው ነው፡፡
ጥብቅ ስፍራው በ15ኛው ክፍለ ዘመን በተተከሉ ሀገር በቀል የሀበሻ
ጽድ ዛፎች ጨምሮ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የተፈጥሮ ደን ከምችት ነው፡፡ ከ167 ዓይነት በላይ የዛፍ ዝርያዎችን አቅፎ የያዘው ሱባ፣
በውስጡ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨት፣ወይራ፣የኮሶ ዛፍ፣የሀበሻ ጽድ እና ሌሎች የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡
የመስህብ ሥፍራው ከ186 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች የሚገኙበት
ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 4ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ዝርያ ናቸው፡፡ በተጨማሪም 38 የዱር አጠቢ እንስሳት በመናገሻ የሚኖሩ
ሲሆን 2ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅየ ናቸው፡፡
ሱባ መናገሻ በውስጡ የሚኒልክ ድኩላ፣ ከርከሮ፣ አነር፣ ነብር እና
ሌሎች እንስሳት የሚገኙበት ሲሆን ከምቹ የአየር ጸባይ ጋር ተዳምሮ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዛ የቱሪዝም መስህብ ነው፡፡
የሱባ መናገሻ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ አከባቢዎችን በአንድ
ሥፍራ ላይ ሆኖ ማየት የሚቻልባቸው የተለያየ ከፍታ ያላቸው ተራሮች አሉት፡፡ ከእነዚህ ተራሮች አንዱ የዳሞቻ ተራራ ሲሆን አንዱ
ውብ የመስህብ ሥፍራ ነው፡፡
ከባህር ጠለል በላይ ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ 385 ሜትር
ከፍታ ላይ የሚገኘው ይህ የሱባ መናገሻ የቱሪዝም መዳረሻ ሀደሬ ፏፏቴን ጨምሮ የተለያዩ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡
በ1975 በሱባ መናገሻ የተገነባው ሙዚየም በውስጡ የተለያዩ
የእንስሳት ቅሪተ አካሎችን ለጎንኝዎች ያሳያል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ሱባ መናገሻ ለመሄድ ሁለት አማራጮችን ሊጠቀሙ
ይችላሉ፡፡ በሰበታ ወይም በሆለታ አድርገው በመጓዝ የሱባ መናገሻ ድንቅ ተፈጥሮን መጎብኘት ይችላሉ፡፡ የሱባ መናገሻ ጥብቅ ሥፍራን
ይጎብኙ ሀገርዎን ይወቁ!!
ምንጭ ዋልታ